የካቲት 09/2013 ዓ.ም
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ
በ1962 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ከአ.አ. በ4ዐዐ ኪ.ሜ ርቀት ላይ በባሌ ዞን ውስጥ ይገኛል፡፡ ስፋቱ ወደ 22ዐዐk.m2 የሚደርስ ሲሆን ከሰሜን ወደ ደቡብ 74 ኪ.ሜ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ደግሞ 53 ኪ.ሜትር ይሰፋል፡፡ ፓርኩ ከባህር ወለል በላይ ከ145ዐ እስከ 4377 ጫማ ባለ ልዩነት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን ያካትታል፡፡ 4377 ጫማ የሚረዝመው እና ከኢትዮጵያ በከፍታው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የቱሉ ዲምቱ ተራራን ጨምሮ የአፍሮ አልፓይን ከፍተኛ ቦታዎች በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የባሌ ተራሮች ከፍተኛ አካባቢ
በተለያየ መንገድ የተፈጠሩ ሀይቆች፤ እርጥበት አዘል መሬቶች የያዘ ነው።
ፓርኩ ከ1600 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፅዋቶች፣ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳትና ወደ 200 የሚጠጉ አእዋፋት በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል 32 ዓይነት ዕፅዋቶች፣ 31 የሚጠጉ ብርቅዬና ድንቅዬ የዱር እንስሳትና ወደ ስድስት የሚጠጉ ዕፅዋት በብሔራዊ ፓርኩ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ዓለም ፈጽሞ አይገኙም፡፡ በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 78 የሚደርሱ አጥቢ የዱር እንሰሳት 17 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙት ብርቅዬ እንሰሳት መካከል ቀይ ቀበሮ፣ኒያላ ፣ አጋዘን እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር ለሳይንስና ኢኮሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው በደረታቸው የሚሳቡ ልዩ ልዩ እንስሳትና መንቆረሪቶችን ፓርኩ አቅፎ ይዟል፡፡ ቡናና በኢትዮጵያ ውስጥ ለባህል መድኃኒትነት የሚውሉ 40 ከመቶ ዕፅዋቶችም ይገኙበታል፡፡ በእፅዋት እና በእንሰሳት ብዝሃ ህይወት መበልፀግ ደረጃ ፓርኩ ከዓለም 34ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የባሌ ብሄራዊ ፓርክ በ “Bird lite International” በዓለም
ከሚገኙ አስፈላጊ የአዕዋፍ መኖሪያ ቦታዎች ጎራ ተመድቧል፡፡
በፓርኩ ከ28ዐ በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች የሚኖሩ ሲሆን ሰባቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡
እንደ ዓለም አቀፍ የወፎች ድርጅት ሪፖርት ከሆነ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የአፍሪካ አራተኛው ‹‹በርዲንግ ሳይት›› ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ በባሌ ብሔራዊ ፓርክ ዋቢ ሸበሌ፣ ዌብ፣ ዱማል፣ ያዶት እና ወልመል የተሰኙ ወንዞች ይፈሳሉ፡፡