ታህሳስ 20/2015 ዓ.ም ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ተጽዕኖ የሚዳስስ በደቡብ ኢትዮጵያ ቱሪዝም መስመር ትኩረት ያደረገ ጥናት ለባለድርሻ አካላት እና ለዘርፉ ምሁራን ባለፈው እሁድ በነበረው የምክክር መድረክ ይፋ አደርጓል፡፡
ጽሁፉን ያቀረቡት የተቋሙ አሰልጣኝ እና የጥናት ቡድኑ አባል አቶ ሳህለ ተክሌ የጥናቱ ዋና ዓላማ ሲገልጹ ደቡብ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ተጽእኖ እና የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት በአቅርቦት፣ በምርትና በገበያ ደረጃ ያለውን ሁኔታ መገምግም፤ የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ተዋናዮች እርስ በርሳቸው የሚቀናጁበትን ሁኔታ ማመላከት ነው ብለዋል፡፡
በጥናቱ የተዳሰሱት አካባቢዎች የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ዋና ዋና ክፍሎች መካከል ያለው ቅንጅት እጅግ አጥጋቢ አለመሆኑ፣ በንግድ ድርጅቶች ውስጥ፣ በድርጅቶችና በአቅራቢዎች መካከል፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለው ትብብር፤ መሻሻል የሚፈልግ መሆኑን የጥናቱ አቅራቢ ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ጥናት የተመረጡት በኢትዮጵያ ደቡባዊ የቱሪዝም መስመር የቱሪስት መዳረሻዎች፤ ላንጋኖ፣ አቢጃታ ሻላ፣ ባቱ፣ ሃዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ፣ ኮንሶ፣ ጂንካ እና አካባቢያቸው ናቸው።
የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ከምርቱ መጀመሪያ አንስቶ እስከ ገበያ ድረስ ባሉ በርካታ ችግሮች ተከቦ ይገኛል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ እንቅፋቶች ቢኖሩም የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት አዳዲስ ሥራዎችንና ለአካባቢው ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለማግኘት የሚያስችል ተስፋ ሰጪ አቅም እንዳለው በጥናቱ ተመላክቷል።
በጥናቱ የአካባቢውን ሀብት ማልማት እና ማሻሻልና ለገበያ ወደሚውሉ ምርቶች ማሳደግ ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት፣የጋራ የቱሪዝም ምርቶችን በማልማት የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ተዋናዮችን ትብብር ማሻሻል የመሳሰሉት ከተሰጡ ምክረ ሃሳቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከተሰጡት ሶስት አበይት ተልዕኮዎች አንዱ የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲውን ኢንደስትሪ በጥናትና ምርምር መደገፍና ክፍተቶችን ለይቶ መፍትሔ ማመላከት ነው፡፡
Recent Comments