ግንቦት 29 /2014 (ኢዜአ)የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮና እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስቦች ቢኖራትም ከዘርፉ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አለመሆኗ ይነገራል፡፡
ለዚህም ዋነኛ ማነቆው በዘርፉ የሰለጠነና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል እጥረት መኖር እንደሆነም ይነሳል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ተክሌ እንዳሉት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትም ዘርፉን በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲመራ እና እንደሀገር የተቀዛቀዘው ን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዚህም መካከል ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት በሙያው እስከ ደረጃ 5 ይሰጥ የነበረውን የክህሎት ስልጠና እስከ ደረጃ 8 ለማሳደግ መታቀዱን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም 9ኛው የቱሪዝም እንግዳ ተቀባይነት ሳምንትን ‘ቱሪዝም ለአብሮነት’ በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 22 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2014 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጆቶች መክበሩንም አንስተዋል፡፡
ቱሪዝም ከአብሮነትና ከሰላም ጋር የጠበቀ ግንኑነት ያለው በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ የሀገሪቱን ሰላም እና የህዝቡን አንድነት ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የቱሪዝም ዘርፉን ሊመሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን በእንግሊዘኛ፤በፈረንሳይኛ እና በጀርመንኛ ቋንቋዎች ጭምር በማሰልጠን ወደ ውጭ አገራት ለማሰማራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ዜጎች እና ሀገሪቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መታቀዱን አስገንዝበዋል፡፡