ክቡር አቶ ንጉሱ ጥላሁን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ
በቱሪዝም ዘርፍ ክህሎት ለሥራ እድል ፈጠራ ያለው ሚና እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በሚል ርዕስ ፓናል ወይይት ተካሄደ፡፡
ቱ. ማ. ኢ ግንቦት 9/2015 ዓ.ም በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት 10ኛው የመስተንግዶና ክህሎት ሳምንት ከትላንት የቀጠለ ፕሮግራም የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የፓናል ውይይት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደተናገሩት ይህ ፕሮግራም ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ችግሮችን ለመፍታት እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ በመነጋገር ችግሮችን ለይቶ መፍትሔውንም ጭምር ያመላከተ ልዩ መድረክ ነው፡፡የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ከ11 ዘርፍ አንዱ እንደሆነና በዚህ ዘርፍ በርካታ ሥራ መፍጠር እንደሚቻል በመጠቆም እንደሚፈለገው እንዳልተሰራም አቶ ንጉሱ ገልጸዋል፡፡
የዛሬው ፓናል ውይይት የክህሎት ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ አንድ ላይ መምጣቱ ሥራ ፈጣሪንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙበት በመሆኑ መፍትሔዎቹ እንደመመሪያ ሊሆኑ የሚችሉ በመሆናቸው በትኩረት መወያየት እንደለባቸው አሳስበዋል፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደገለጹት ትላንት የተጀመረው 10ኛው የመስተንግዶና ክህሎት ሳምንት አካል የሆነው የፓናል ውይይት ተቋሙ ከመንግስት የተቀበለውን ሀገራዊ ግቡን ለማሳካት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በማመን ከውይይቱ ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠርና የመንግስት ፖሊሲ ላይ ማስተካከያየ ሊያሰጥ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ፓናሊስቶቹ ከተለያዩ ዘርፎች ከግል ድርጅቶች እንዲሁም ከመንግስት የተወጣጡ ሲሆኑ አቶ መላኩ ሲማ ከአዲስ አበባ ሆቴሎች ባለቤቶች ማህበርና የሂልተን ሆቴል አስተዳደር፣ አቶ ነጋ ወደጆ ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ፣ ዶ/ር ገነነ አበበ ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት፣ አቶ ንጉሴ እንግዳወርቅ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ አቶ ቦሩ ሻና ከኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት፣ አወያዩ ዶ/ር ሙሉጌታ አስተርአየ ናቸው፡፡ የፓናል ውይይቱ የቱሪዝም ክህሎትና የሥራ እድል ፈጠራ ያለው ሚናና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን በተመለከተ ሁሉም በቂ የሆነ ከተሞክሮና ከሙያ አኳያ ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ሊሰሩ የሚገባቸውንና ክፍተቶቹን በመለየት ሰፊ የውይይት አድርገዋል፤ ከቤቱም ለተነሱት ሀሳቦች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ክቡር አቶ ንጉሱ ጥላሁን የፓናል ውይይቱን ሲያጠቃልሉ በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ ዙሪያ በስልጠና መሸፈን ያለበትን፣ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች መሸፈን ያለበትን፣ ከውጭ የምናስመጣቸውን ባለሙያዎች ለምን ያህል ጊዜ ዕውቀትን እና የሥራ ባህልን ማሻገር ይችላሉ የሚሉ ሃሳቦች እና በዘርፉ ላይ የሚነሱሃሳቦችን እርሳቸው የሚመሩት የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ገበያ ልማት ዘርፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባው ከፓናል ውይይቱ ግብዓት እንደወሰዱ፤ ይህ መድረክ ዓመት ጠብቆ መካሄድ የለበትም በቅርበት ተገናኝቶ ሀሳብ እየተለዋወጡ ሥራን እየገመገሙ መሄድና ክፍተቶችን ማጥበብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡