የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ይፋዊ የማብሰሪያ ስነ-ሥርዓት ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ በስትራቴጂው የትኩረት አቅጣጫዎችና ዝርዝር አላማ ዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ስትራቴጂ በዘመናዊ ክህሎቶች የተካነ፣ ሥራ ፈጣሪና ሀገር ወዳድ የሆነ ትውልድ የማፍራት ዓላማን ያነገበ መሆኑን ገልጸዋል። የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አስተዳደርን ማጠናከር የስትራቴጂው ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው የባለድርሻ አካላትን እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማጠናከር ፣ የዜጎችን ተሳትፎን ተቋማዊ ማድረግ፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን መሰረተ ልማትን ማሻሻልና ማሳደግ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርአትን ማዘመን በስትራቴጂው በዋነኝነት ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አግባብነት እና ጥራትን ማሻሻልን በተመለከተም በማህበረሰብ የስልጠና ፍለጎቶችን የመለየትና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት የክህሎት ክፍተቶች ላይ ተመስርቶ የሚመራበት ስርዓት እንደሚዘረጋም አስታውቀዋል፡፡
የብቃት ምዘና እና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ስርዓቱን ማዘመን፣ ተቋማት አካባቢያዊ ፀጋዎቻቸውን የለየ የስልጠና ፕሮግራሞችና ሙያዎች ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻል፣ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓት ጋር ማዋሃድም በስትራቴጂው ውስጥ በልዩ ሁኔታ የተካተቱ ተግባራት መሆናቸውን ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
ለሥራ ዝግጁ የሚያደርጉ ክህሎቶችን ማዳበር ሌላው በስትራቴጂው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደመሆኑ ማህበረሰቡን መሰረት ያደረጉ የሥራ ላይ ልምምድና ትብብር ስልጠናዎች የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠራም ተገልጿል፡፡
ሀገራዊ የክህሎት ባንክን በማቋቋም የክህሎት ክምችትና ዝውውር ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ በገለፃቸው ያብራሩት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በአለም አቀፍ የሥራ ገበያ ላይ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት በሚያስችል መልኩ የሥልጠና ጥራትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረትና ዜጎች በልምድ ላገኙት ክህሎት እውቅና ከመስጠት አንፃር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡
ምርምር ፣ፈጠራና የማህበረሰብ አገልግሎት ሌላው የስትራቴጂው የትኩረት አቅጣጫ ሲሆን ፈጠራና ኢኖቬሽንን ማበረታታት፣ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ማስፋፋትና ማጠናከር ፣ በተሰጥኦ ላይ የተመሰረተ የስልጠና እና የምደባ ስርዓትን መተግበር ብሎም ተሰጥኦንና መለየትና ማዳበር የመሳሰሉት አጀንዳዎችም በዚህ የትኩረት አቅጣጫ ስር እንደተካተቱ አስረድተዋል፡፡
ህዳር 6/2018 ዓ.ም ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ለወቅታዊ ትኩስ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
Official Website: mols.gov.et
Facebook: https://web.facebook.com/MolsFDRE
Telegram: t.me/fdre_mols
TikTok: tiktok.com/@mols_official
Twitter / X: twitter.com/Jobs_ሚኒስቴር
WhatsApp: whatsapp.com/channel/0029VakCgcYIyPtTbPZtDW1y