ሆ.ቱ.ስ.ማ.ኢ ጥቅምት 27/28 /2012 ዓ.ም
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደር በሆቴልና ቱሪዝም ስልጠና ለመውሰድ ፍላጎት ከነበራቸው ሰልጣኞች መስፈርቱን ያሟሉ ከ500 በላይ የቀን መርሃ ግብር ሰልጣኞች የተቋም ትውውቅ አካሄደ፡፡
በትውውቅ ፕሮግራሙ የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ዘንድሮ የተቀበልናቸው ሰልጣኞች በተቋሙ ታሪክ 51ኛ መሆናቸውንና የሆስፒታሊቲ ኢንደስትሪ 50 ዓመታትን በብቃት ያሰለጠነ ለሌሎች መሰል ተቋማት መፈጠር የበኩሉን አስተዋጽኦ ወደ አበረከተው አንጋፋ ተቋም እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡
የሆስፒታሊቲ ኢንደስትሪ የሚፈልገውን ሙያዊ ስነምግባር አሟልታችሁ እንደቀደምት የተቋሙ ሰልጣኞች መልካም ስም ያተረፋችሁ እንድትሆኑ ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅባችኋል ካሉ በኋላ ሰልጣኞች በሁሉም ዘርፍ በርትቶ በመማርና በሚያጋጥሙ ችግሮች ሳይደናቀፉ ስኬታማ ባለሙያ ለመሆን መትጋት እንዳለባቸው በመግለጽ የግቢ ቆይታቸው መልካም እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡
የተቋሙ አካዳሚክና ምርምር ዲን አቶ ግሩም ግርማ በበኩላቸው የዘንድሮ የተማሪ ቅበላ ከሌሎች ዓመታት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ የጨመረና መንግስት አዲስ በተቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት የሚማሩ መሆናቸው እድለኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ኡማ ከሰልጣኞች ስለሚጠበቀው ተግባርና ኃላፊነት ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በሰነዱ መነሻነት ከሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ከትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና ከአካዳሚክ ዲን ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡
ምላሽ ቢሰጥም በቂ አይደለም ያሉት በወር የሚከፈለው የኪስ ገንዘብ ዝቅተኛ መሆንና የደንብ ልብሰ ለማሰፋት ካለው ኑሮ ውድነት ጋር ከፍተኛ ችግር መሆኑን ሰልጣኞች ተናግረዋል፡፡ ይህን የገለፁት ከተለያየ ክልል መጥተው አዲስ አበባ ውስጥ ቤት ተከራይቶ፣ ምግብ በልቶ ለመኖር እና የትምህርት ቁሳቁስን ለማሟላት 510 ብር በቂ ነው ብለን ስለማናምን ቢያንስ ዶርም እንኳ ማግኘት ቢቻል የሚል አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እንደ ተቋማችን ነባራዊ ሁኔታ እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም መንግስት ካስቀመጠልን በጀት በላይ መክፈል የማንችል ስለሆነ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ትኩረት እንዲያደርጉበት ጥሪ ማቅረብ የተቋሙ ድርሻ ይሆናል፡፡
ለሰልጣኞች የተዘጋጀው የትውውቅና የቅድመ ዝግጅት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት የቀድሞ ተማሪዎች የማነቃቂያና የተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ ለሰልጣኞቹ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት በግቢው ውስጥ የሚኖራቸው ጊዜ የተሳካ እንዲሆንና በማንኛውም ጊዜ የሚኖራቸውን ጥያቄ በኢንስቲዩቱ ያሉ አመራሮችና መምህራን ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንዳይሉ ቆይታቸውም የተሳካ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡