ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ኢ መጋቢት 27/ 2011 ዓ.ም
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች “ከመጋቢት እስከ መጋቢት” የተቋሙን የአንድ ዓመት ጉዞ አስመልክቶ መጋቢት 26/2011 ዓ.ም በገነት ሆቴል ውይይት አካሄዱ፡፡
በሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አሰቴር ዳዊት ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በየደረጃዉ የሚገኙ ሠራተኞች የበኩላቸውን ድርሻ በንቃትና በትጋት በጋራ ተባብሮ መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
ለተቋሙ ሠራተኞች “ከመጋቢት እስከ መጋቢት” ባሉት ጊዜያት እንደ ሀገር አቀፍና በተቋም ደረጃ የተመዘገቡ አዎንታዊና አሉታዊ ጉዳዮች በቀረበው መነሻ ጽሁፍና የዘጠኝ ወር የቁልፍ ተግባራትና አበይት ተግባራት አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ተቋሙ ለ50 ዓመታት በዘርፉ ሰለጠነ የሰው ሀይል የሚያቀርብ ብቸኛ የመንግስት ተቋም ቢሆንም እንደ አድሜው አንጋፋነት አሁን ያለበት ደረጃ አመርቂ ባለመሆኑ መመህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች መሻሻል አለባቸው ያሉት ጉዳዮችን አንኳር አንኳር ነጥቦች አንስቷል፡፡
ውይይቱ በተለይ የፋይናንስ አፈጻጸማቸን ከማዕቀፍ ግዥ ጋር በተያያዘ በመጓተቱ ምክንያት የታቀደውን ያህል መሄድ አለመቻሉ የተገለጸ ቢሆንም ቀጣይ ባሉት ጥቂት ጊዜያት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደምሰሩ የአስተዳደርና ልማት ዲን አቶ ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል፡፡
የተቋሙ የከፍተኛ ትምህርት ማዕቀፍ ረቂቅ ደምብ ረጅም ሂደት እየወሰደ እንደሆነና በአሁኑ ጊዜም ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተሸሻለ ረቂቅ ደምብ ለሚኒስትሮች ምክርቤት አስገብቶ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የአካዳሚክና ምርምር ዲን አቶ ግሩም ግርማ ገልጸዋል፡፡
በማጠቃለያው ወ/ሮ አስቴር ዳዊት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር የቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ገንቢ በመሆናቸው የተሻለ አፈጻጸም ለማምጣት በጋራ እንረባረባለን ብለዋል፡፡