የካቲት 28/2015 ዓ. ም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አሰልጣኞች በሸራተን አዲስ ሆቴል የተግባር ስልጠና ጀመሩ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በስልጠናው ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተገኝተው እንደገለጹት ሸራተን አዲስ ሆቴል ለተቋማችን አሰልጣኞች ይህን መሰል ስልጠና ሲሰጥ የመጀመሪያው አይደለም፤ ዛሬም ይህን ስልጠና እንዲያገኙ ለአሰልጣኞቻችን በማመቻቸቱ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለወጣት ለሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ ምስጋና አለኝ ብለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው እንዳሉት መንግስት ሁሉን መስራት፣ ሁሉን ማሟላት አይችልም፤ስለሆነም የግሉ ዘርፍ በየተሰማራበት የሙያ መስክ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ለዚህ ደግሞ ሸራተን አዲስ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡
አሰልጣኞቻችን በዚህ ዘርፍ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ አይተው በተግባር ሰልጥነው ለሰልጣኞቻቸው እውቀትና ክህሎታቸውን የሚያጋሩበት ምቹ ጊዜ በመሆኑ የተሰጣቸውን ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ ዋና ዳይሬክተሩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የሸራተን አዲስ ሆቴል ጄኔራል ማናጀር ሚስተር አንቶኒ በበኩላቸው ኢንደስትሪውን ለማሳደግ እንደ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ያሉ የስልጠና ቋማት አሰልጣኞች የሪፍሬሽመንት ሥልጠና በየጊዜው መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ይህን ለማድረግ ደግሞ እኛ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
ሚስተር አንቶኒ አክለውም አሰልጣኞች ሁልጊዜ ከዘርፉ ቴክኖሎጂዎች ጋር ራሳቸውን ብቁ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ እነሱ ያሰለጠኑትን ነው እኛ የምንወስደው በዚህ ሽግግር ደግሞ እኛ ብቻ ሳንሆን ሀገርም ተጠቃሚ ናት ብለዋል፡፡
ስልጠናው በቤት አያያዝ፣ በትኩስ መጠጦች ዝግጀት፣ በምግብ እና መጠጥ ዝግጅት፣ ለአምስት ቀናት እንደሚቆይ ከስልጠና አስተባባሪዎቹ ተገልጿል፡፡