በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከKFW እና ከIP አማካሪ ድርጅት ከመጡ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ጋር ኢንስቲትዩቱን የልህቀት ማዕከል ማድረግ ላይ ውይይት አደረገ።

በዛሬው እለት ተቋሙ ያለበትን ሁኔታ በመረዳት የልህቀት ማእከል ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ የሚያገኝበትን ውይይት ከሚስ ጂያኒን ሴትዘር ረብረክ KFW የጀርመን ልማት ባንክ ምክትል ዳይሬክተርና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ከፍተኛ ፕሮጀክት ኤክስፐርት እና ዶ/ር ሮበርት ናስር በአዲስ አበባ የIP አማካሪ ቡድን መሪ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ውይይት አድርጓል።
በኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ከተደረገ በኋላ በኢንስቲትዩቱ አካዳሚክና ምርምር ዲን ከታሪካዊ አመጣጡ እስከ አሁን ያለበትን ተቋማዊ ሁኔታ የውይይት መነሻ ሀሳብ ቀርቧል።
በመቀጠልም ተቋሙ ያሉትን የሥልጠና ቦታዎች እንዲጎበኙ በማድረግ ከጉብኝቱ በኋላ በውይይት ወቅት ተጨማሪ ሀሳቦች በምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ገዛኸኝ አባተ፣ በትምህርት ክፍል ሃላፊዎች እና መምህራን በኢንስቲትዩቱ ያለውን ምቹ ሁኔታና ችግሮችን የገለፁ ሲሆን ተቋሙን የልህቀት ማእከል ለማድረግ የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ሚስ ጂያኒስ እንደገለፁት በዛሬው እለት ያየነው ተቋም የመንግስትና የእኛም ድርጅት ትኩረት ያለው ልንደግፈው የምንፈልገው ዘርፍ ስለሆነ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በምናደርገው ስምምነት ወደ ሥራ እንገባለን በማለት እንደኢንስቲትዩት መሥራት የሚጠበቅብንን ተግባራት በግልፅ በመግባባት ውይይቱ ተጠናቋል።