አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ በተማሪዎች መካከል የሚካሔደው የክህሎት ውድድር ዘርፉን መምራት የሚችል ብቃት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራት እንደሚያግዝ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለፁ። አራተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር እና 12ኛው የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ማስጀመርያ መርኃ ግብር ተከናውኗል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ እንዲሁም የቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
አቶ ሰለሞን ሶካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በየጊዜው የሚካሔደው የክህሎት ውድድር በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራት ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው።

በክህሎት ውድድሩ የሚሳተፉ ተማሪዎች የተሻለ አቅም ይዘውና ነጥረው እንዲወጡ የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎቹ በሀገር እና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እድል እንዲኖራቸው እንደሚያስችልም ነው ያሉት።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የቱሪዝም ዘርፉ ክህሎት ባላቸው ዜጎች እንዲመራ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
አራተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር እና 12ኛው የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት “ብሩህ አእምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ሚያዝያ 21 እና 22 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።
#Ethiopia
#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ