ሚያዚያ 4/2014ዓ/ም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ከጀርመን ኤምባሲ ጋር በመተባበር የግሉ ዘርፍና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር ምድረክ ተካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር በከር ሻሌ የጀርመን መንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ለማገዝ የሚያደርገውን ጥረት በማመስገን በዘርፉ የተሰማሩ የሆቴልና ቱሪዝም ባለሃብቶችና ድርጅቶች ከማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የጀርመን ትብብር ልማትን ወክለው ንግግር ያደረጉት ቤንጃሚን ሀከር ኢትዮጵያ በቱሪዝም ብዙ ሀብት ያላት ሀገር በመሆኗ ዘርፉን በብቁ ባለሞያዎች በማሳደግ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ገልፀው የጀርመን መንግስትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ሃሳባቸውን ከገለጹት መካከል የሃያት ኢንተርናሽናል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሄዶ ሰብ “ሆቴሉን ከከፈትን በኋላ የመጀመሪያ ጥያቄያችን የነበረው በሙያው የስለጠነ ባለሙያ ለማገኘት የምንችልበት የማሰልጠኛ ተቋም አለወይ? የሚል ነበር፤ በቀድሞ ስሙ የሆቴል እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትን ካገኘን በኋላ በርካታ ሥራዎችን አብሮ መሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰምምነት በመፈራረም 30 በምቶ የንድፈ ሃሳብ ሥልጠና 70 በመቶ የተግባር ሥልጠና ላይ በማተኮር ሰልጣኞችን በመደልደል 60 ዎቹን ወስደን ወደ ተግባር የገባንበት ትልቅ ተሞክሮ ነው” ሲሉ ልታዳሚው ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
ሁሉም አቅራቢዎች ከሥልጠና ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው ያለንን ወጣት ኃይል በመጠቀም የተሻለ ባለሙያ፣ ጥራት ያለው ሥልጠና በመስጠት ከአገር ውስጥ ፍላጎት አልፎ እንደሌሎች አገራት ወደ ውጪ መላክ የሚያስችል ብቃት ሊኖር ይገባል በማለት የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የተቋሙ አካዳሚክ እና ምርምር ዲን ከስልጠናና ሌሎች የትብብር ሥራዎችን በተመለከተ ምላሽ ተሰጥተዋል፡፡
የተቋማችን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ለጀርመን ኤምባሲ ይህን ፕሮግራም በባለቤትነት በማዘጋጀታቸው አመስግነው ከመድረክ ለተሰጡ ሃሳቦችና ለተሳታፊዎች ምስጋና ካቀርቡ በኋላ ‘መተጋገዝ ፣ ተባብሮ መሥራት አብረን እንዳንወድቅ ይረዳል’ በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ ገዛኽኝ ይህን መሰል የመማማሪያ መድረክ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም እንዲተባበር በማሳስብ የጀርመን ኤምባሲን እና የሚኒስትር መ/ቤቱን ኃላፊዎች በድጋሚ አመስግነዋል፡፡