የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የ10ኛው የመስተንግዶና የክህሎት ሳምንት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ከመክፈቻ ፕሮግራሙ ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋሙን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት የምግብ ዝግጅትና የመስተንግዶ ውድድሮች፤

የቱሪዝም ሰልጣኞች የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በጀርመንኛ ያካሄዱት ውድድር፣ በርካታ ሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች የተሳተፉበት ጆብ ፌር እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እጅጉን የደመቀበት ዐውደ ርዕይ፤ በሁለተኛው ቀን የፓናል ውይይት እና ለተሳታፊዎች እና ለተወዳዳሪዎች ሽልማት እና የምስክር ወረቀት በመስጠት ማጠቃለያውን አድርጓል፡፡
በዚህ ማጠቃለያ ፕሮግራም የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደተናገሩት ዛሬ ስልጠናው የሚፈልገውን ማንኛውንም መስፈርት አሟልታችሁ የተሸለማችሁ እንኳን ደስ አላችሁ! ነገርግን ኃላፊነት አለባችሁ፤ ሽልማቱ አደራ ነው፤ በሙያችሁ ተፈላጊ ለአገርም የምትተርፉ፣ ተተኪ የምታፈሩ እንድትሆኑ እንጠብቃለን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚያዘጋጀው አገር አቀፉ ክህሎት ለተወዳዳሪነት በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚከናወኑ ውድድሮች ማጠቃለያቸው ከሰኞ ግንቦት 14/2015ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን የምግብ ዝግጅት እና መስተንግዶ ላይ ያሉ ተወዳዳሪዎችን በተቋማችን የምናካሂድ ይሆናል፡፡