ቱሪዝም ለሥራ ዕድል በሚል መሪ ቃል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከሰመራ ዩንቨርሲቲና ከአፋር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በሰመራ ያካሄደው 10ኛው ዙር የምርምር ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት አጠናቀቀ ፡፡
የኮንፈረንሱ አካል የሆነው የክልሉን ተፈጥሯዊና ባህላዊ እንዲሁም ታሪካዊ ቦታዎች በባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስተባባሪነት ጉብኝት የነበረ ሲሆን የአዋሽ ወንዝ የመጨረሻ ጉዞ የሚያጠናቅቅበት የገመሪ ሃይቅ የሚገኝበትን ሥፍራ ቅድሚያ ተጎብኝቷል፡፡
ይህ ሀይቅ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የዓሳ ዓይነቶችና አዞ በብዛት ይገኝበታል፡፡ የአፋምቦ ሀይቅ ከገመሪ ሀይቅ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሲሆን አፋምቦ የወረዳው መጠሪያም ሆኖ ያገለግላል፡፡
ሌላው የጉብኝቱ አካል የነበረው በጣሊያን ወረራ ጊዜ የተገነባ እንደ እስር ቤት በኋላም በፈረንሳይና የአፋር ሱልጣን መካከል ጦርነት የተደረገበት ጊዜ እንደ ካምፕ ይጠቀሙበት የነበረ ታሪካዊ ሥፍራ ነው፡፡
ሥፍራው ከፍታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ጠላትን ለመከላከል እና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር መስዋዕትነት የተከፈለበት በተለይም ለጅቡቲ ቅርብ እንደመሆኑ በተደጋጋሚ ፈረንሳዮችም በዚያ ለመግባት ሙከራ አድርገው ጀግኖቹ የአፋር አባቶቻችን ጋር ጦርነት እየገጠሙ አፍረው መመለሳቸውንም ያየንበት ድንቅ ቦታ ነው፡፡
በመጨረሻም የአፋምቦ ወረዳ ማህበረሰብ የቴምር እርሻ በሚገኝበት ለምለም ሥፍራ በባህላዊ ጨዋታ እና በባህላዊ ምግብ እንግዶችን አስተናግደዋል፡፡
የኮንፈረንሱ አዘጋጆች ሶስቱም ተቋማት ለተደረገላቸው አቀባበል ካመሰገኑ በኋላ አካባቢው ያለውን የቱሪዝም ሃብት ለማልማትና ወጣቱን ሥልጠና በመስጠት ተጠቃሚ ለማድረግ የየድርሻቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ይህን መሰል የምርምር ኮንፈረንስ ባለፈው ዓመት ከባህርዳር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባባር ባህርዳር ላይ ማዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡
Recent Comments