ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ኢ ነሐሴ 28/2011 ዓ.ም
በሀገራችን የምስራቁ ክፍል ከአዲስ አበባ በ526 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ሐረር 343.2 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ያቀፈች ጥንታዊት ከተማ ናት። በሀረሪ አደርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ ፣ ትግርኛ፣ ጉራጌኛ እና ሱማሌኛ ቋንቋዎች ይነገሩባታል።
ሀረር በቀደምት ታሪካዊና ጥንታዊ የስልጣኔ ከተማነቷም ትጠቀሳለች። በከተማዋ ውስጥ በሚገኘው የጁገል ግንብ ውስጥ የጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫዋ ከሆኑት ባህላዊ ቤቶች እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ይገኛሉ፡፡ ግንቡ አምስት በሮች ያሉት ሲሆን ከሐረሪ ቋንቋ በተጨማሪም በአረብኛ፣ በአማርኛና በኦሮምኛ ስያሜ መጠሪያዎች አሏቸው። የጁገል ግንብ በከተማዋ ይሰነዘሩባት የነበሩ ጥቃቶችን ለመከላከል በሚል መገንባቱን ታሪክን አጣቅሰው ብዙዎች ይናገራሉ። ሆኖም ዛሬ ላይ ቅርሷ ለመሆን ሚና ተጫውቷል።
ሐረር በአንድ ወቅት የራስዋ መንግሥትም ኖሯት ታስተዳድር እንደነበረች፤ በወቅቱም የራስን የመገበያያ ሳንትም በማሳተም ስትጠቀም እንደነበረች አሁን በሙዚዬሞቹዋ ውስጥ የሚገኙ የድሮ ሳንትሞችና ስለ ሀረር የተጻፉ የታሪክ ድርሳናት ህያው ምስክር ናቸው፡፡
ሐረር ለአንድ ሺህ ዓመታት የቆየች እድሜ ጠገብ ከተማ ስትሆን በዚህ ጊዜ ውስጥም አራት ስርወ መንግሥት ያሳለፈችና 72 ነገስታት የነገሱባት ናት፡፡
በከተማዋ ውስጥ የማህበረሰቡ የቤት አሰራር ጥበብ ጥንት ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውና በየትኛውም የሀረሪ ብሄረሰብ ዘንድ የሚሰሩ ቤቶች ተመሳሳይነት ያላቸውና ከድንጋይና ከእንጨት ሲሆን የቤት መስሪያው ድንጋይ በሀ ድንጋይ የሚባል ነው፡፡ ጣሪያው በጥድ ወይም በዋንዛ እንጨት ይሰራል። በዚህም ከቤት ውጪ ከፍተኛ ሙቀት ሲኖር ቤቱ ውስጥ ሙቀቱ አይሰማም፡፡ የሐረሪ ቤት ከፊት ከሚታየው ክፍል በተጨማሪም ሌሎች ሁለት ክፍሎት አሉት። አንድ ፎቅም አለው። በቤቱ ውስጥ እንደሚሰጡት አገልግሎት ስያሜና ትርጉም ያሏቸው አምስት ለመቀመጫነት የሚያገለግሉ መደቦች ይገኛሉ።
ቤቱ ሁለት ምሰሶዎች አሉት። በአምስት የመቀመጫ መደቦች የተከፋፈሉ ናቸው። የንጉስ መደብ የቤቱ አባወራ የሚቀመጥበት፣ ትልቁ መደብ የተማሩ ሰዎች የሚቀመጡበት ሆኖ በዚሁ ቦታ ላይ ትምህርት ያስተምሩበታል። ሌላው ሽማግሌዎች የሚቀመጡበት መደብ ነው። ትንሿ መደብ ወጣት ወንዶች የሚቀመጡበት ሲሆን ከበሩ ጀርባ ያለው መደብ የእናቶች መቀመጫ ነው። ወለሉ ላይ ህጻናት ይቀመጣሉ።”
በሀረሪ የቤት የውስጥ ገጽታን ለማስጌጥ የሚጠቀሙበት በሀረሪ ሴቶች የሚሰሩ የተለያዩ የስፌት ስራዎች አሉ። ጥቂቶቹም በቤቱ ግድግዳ ሲሰቀል ትርጉም አላቸው።
ሰሀኖች፣ በእንጨት የተሰሩ ቆሪዎች፣ ስፌቶች፣ ሌማት ፣ ወስከንባ የተለያዩ ስፌቶች በግራና በቀኝ ይሰቀላሉ።
በጁገል ግንብ ውስጥ ከሰማንያ ሶስት በላይ መስጅዶችና በ1890 ዓ.ም የተሰራው የመድኃኒያለም ቤተክርስትያን፣ የተለያዩ ሙዚዬሞች ይገኛሉ፡፡ በግንቡ ውስጥ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ተብሎ የሚነገርለት የልብስ ስፌት ስራ ተጀመረበት የልብስ ስፌት ስንጄሮች የሚገኙበት መኪና ግርግር የሚባል ሰፈር ይገኛል፡፡ ጭልፊቶች ከሰው እጅ ስጋ ወስዶ የሚበሩበትና ጅብ በአፍና በእጅ የሚያበሉበት ሁኔታዎችም ሀረርን ልዩ ያደርጋታል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሰራተኞች፣መምህራንና የስራ ሃላፊዎችም ከቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችና የሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታዎችን ለማየትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ወደ ከተማዋ በመሄድ ቆይታ አድርገዋል፡፡
በዚህም በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት ለቀጣይ የቤት ስራ እንደተወሰደ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ተክሌ ገልጸዋል፡፡
#በብሩክታደሰ