የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሰራተኞች የሀገራችንን ወቅታዊ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በተግባር እንዲረዱት የሚያስችል ትምህርታዊ ጉብኝት አድርገዋል። በሀገራችን ቱሪዝም እድገት ውስጥ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት የበኩሉን አሻራ ያሳረፈው አንጋፋው ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ሠራተኞቹም ወቅቱን ያገናዘበ መረጃ እንዲኖራቸው የሚያደርግ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እና ሌሎችም የቱሪስት መስህቦችን ጎብኝተዋል፡፡

ከታዩት መስህቦች መካከል በፓርኩ የሚገኙ ሀይቆችና ፏፏቴዎች፣ ዝሆን እና ሌሎች አጥቢ እንስሳትና አዕዋፋት ይገኙበታል፡፡
ፓርኩ ኢትዮጵያ ካሏት ድንቅ ተፈጥሮ ሀብቶች ልዩ የሆነ፣ በገበታ ለሀገር መርሐ ግብር የዝሆን ዳና ሎጅ የተሰራበት እና ሌሎችም በርካታ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪና መሰረተ ልማቶች በግል ባለሀብቶች እየተሰሩበት ያለ ፓርክ ነው፡፡
ሰራተኞቹ ጉብኝቱን በመሄዳቸው እርስ በራስ ያለንን መተሳሰብን እና አብሮ መቆምን አጠናክሮልናል፣ የሀገራችንን ቱሪዝም በተጨባጭ ሁኔታ እንድናውቅ ረድቶናል ፣ ለማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ሰጥቶናል ብለዋል፡፡
አስደናቂ የተፈጥሮ ሀብቶችን የያዘው ይህ ግዙፍ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፣ በዳውሮ እና በኮንታ ዞን ተዋስኖ ይገኛል፡፡
ብሔራዊ ፓርኩ በ1997 ዓ.ም በብሔራዊ ፓርክ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን ፓርኩ የሚያካልለው የቆዳ ስፋት 1 ሺህ 410 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን ከአዲስ አበባ በ475 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ፓርኩ የግዙፉ የአፍሪካ ዝሆን መኖሪያም ሲሆን በውስጡ ከ800 በላይ የሚሆኑ ዝሆንና ከ5 ሺህ በላይ ጎሽ የሚገኝበት መሆኑ ፓርኩን ልዩ ያደርገዋል፡፡
ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ በባቱ- ቡታጅራ- ወላይታ ሶዶ ተርጫ-አመያ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ወይም በጅማ መስመር በሁለት አማራጮች መጎብኝት ይቻላል፡፡
የጉብኝት ጊዜ ቢያንስ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ሊወስድ የሚችል ሲሆን የአካባቢውን ውብ ተፈጥሮን እያደነቁ ፣ ፍራፍሬ እየተመገቡ፣ እየሸመቱ የሚጓዙበት ድንቅ ጉዞ ነው፡፡
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et