የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እና እሴት ሰንሰለቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ የአጋርነት ስምምነት ከቦስተን ፓርትነርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ኩሪፍቱ ሪዞርት) ጋር ተፈራርመን ወደ ሥራ መግባታችን ይታወሳል፡፡
ይህ አጋርነት ፍሬ አፍርቶ በመስኩ በትብብር ስልጠና መስጠት ተጀምሯል፡፡
ኩሪፍቱ አፍሪካ ቪሌጅ የአፍሪካ ሀገራትን ባህል፣ ወግ እና እሴት የሚያስተዋውቁበት መርሃ ግብር ቀርጾ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመት “የኢትጵያ ወር” በሚል ስያሜ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡
ይህም በዘርፉ ያሉንን እምቅ አቅሞች አውጥቶ ከማስተዋወቅ ባሻገር በእሴት ሰንሰለት ውስጥ በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ብሎም በትውልዶች መካከል የክህሎት ሽግግር ማካሄድ ያስችላል::
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሀገራችን ባህላዊ ምግብና መጠጦች ወደ ገበያ ለማስገባት እና የሆቴል የምግብ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ባደረገው ጥናት ከሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች 32 በላይ የሚደርሱ ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን ለይቶ የሆቴል የምግብ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በእስከ አሁኑ ሂደትም በ 4 ትልልቅ ሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ማካተት ተችሏል፡፡
ዛሬ በኩሪፍቱ አፍሪካ ቪሌጅ ያስጀመርነው የመጀመሪያው የባህላዊ ምግብ ፌስቲቫል የዚሁ ሥራ አካል አካል ነው፡፡ ወሩ በኢትዮጵያ የተሰየመ እንደመሆኑ ፌስቲቫሉ ለሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት ባህላዊ ምግቦቻችንን እያስተዋወቀ ይቀጥላል፡፡
የቦስተን ፓርትነርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ኩሪፍቱ አፈሪካ ሪዞርት) መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው አጋርነታችንን ለማጠናከርና በዘርፍ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማስፋት እያደረጉ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ከልብ የመነጨ ምስጋናዬ ይድረስዎ!
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የኢንስቲትዩቱ መላው አመራርና ባለሙያዎች ለመርሃ ግብሩ ስኬት ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡
የሥራ ባለቤት እርስዎ ነዎት!

Recent Comments