ቱማኢ ታህሳስ 25/2025 ዓ.ም ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ከአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ጋር በመተባበር፣ በከተማዋ ለሚገኙ ሆቴሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃታቸውን የሚያሳድግ የማማከር አገልግሎት መስጠት ጀመረ። አገልግሎት አሰጣጡን አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም እና የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የማማከር አገልግሎቱ ባለሙያዎች በየሆቴሎቹ ተገኝተው የአሰራር ክፍተቶችን በተግባር የሚያርሙበት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በከተማው የሚገኙ 63 ባለኮከብ ሆቴሎችን አገለግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል ተብሏል።
በማማከር አገልግሎቱ ከሆቴሎቹ ውጫዊ ገጽታ ጀምሮ የእንግዳ መቀበያ፣ የምግብ ዝግጅት፣ የመኝታ ክፍሎች አያያዝ እንዲሁም የምግብና መጠጥ መስተንግዶ ክፍሎችና የጽዳት አጠባበቅ በዝርዝር እንደሚፈተሽ ተገልጿል።
አገልግሎቱ አሁን መስጠት ያስፈለገበት ዋና ጉዳይ መጪውን የገና እና የጥምቀት በዓላትን ተከትሎ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ሀገር ቤት የሚገቡበት ወቅት በመሆኑ፣ ሆቴሎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም በከተማዋ የሚስተናገዱ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በብቃት ለማስተናገድ የሆቴሎችን ዝግጁነት ከፍ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል።
ለዚህም ሥራ ከሁለቱ ተቋማት የተወጣጡ 12 ከፍተኛ ባለሙያዎችና ሱፐርቫይዘሮች ተመድበዋል።
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et


Recent Comments