ቱ. ማ. ኢ ግንቦት 8/2015 ዓ ም በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት የዘንድሮው የክህሎትና የመስተንግዶ ሳምንት በዘርፉ ውስጥ የሚገኙትን ተዋንያን የሚያሳትፍ ውድድር መጀመራችሁ አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን በአስተማማኝ ሁኔታ በመቅረፍ የኢትዮጵያን ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስችላሉ ተብለው በመንግስት ከተለዩት አምስት ቁልፍ የልማት መስኮች አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ይህ ዘርፍ የሀገር አምባሳደር የሆነ ኢትዮጵያን አንድ ቀን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደረግ፣ ዜጎችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል የአምባሳደርነት ሚና ያለው ቱሪዝም ብቻ ነው።
ዘርፉ ያለውን ዕምቅ ሀብት ገና አልነካነውም፤ ልጆቻንን በትልልቅ ሆቴሎች ማየት ከሀገር አልፈን የውጭ ሀገራትን ገበያ መሸፈን እንሻለን፤ ለዚህ ደግሞ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። ሀገር በቀል ዕውቀትና ክህሎቶችን ከዘርፉ እድገት ጋር አስተሳስረን የምንጠቀምበት ጊዜ ላይ ነን።
ባለፈው ዓመት በአገልግል የተመሰለ ኬክ ቀርቦ ነበር፤ ዘንድሮም በተቋሙ ወርቅ እጆች የተሰራ የቡና አቀራረብ ስርዓቱን በኬክ ተሰርቷል። ይህንን በስልጠና ብናግዘው አደባባይ ቢወጣ በምግብ ዘርፉ ላይ ብቻ የሚሰራው ሥራ በጣም ትልቅ ነው።
ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ኬክ ወዘተ ለየብቻው እራሱን የቻለ ነው። ባህላዊ መጠጦችን በእናቶች የሚሰሩት እምቅ ሀብት ናቸው። የእኛን ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን በባለአምስት ኮኮብ ላይ ማግኘት አለብን።
እንግዳ ተቀባይነታችንንና ሰው አክባሪነት ከዘርፉ ጋር አስተሳስረን ብናለማው ተገልጋዮችን መጨመር እንችላለን።
ክቡር አቶ ጌታቸው ነጋሽ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ዘንድሮ የምናከብረው የመስተንግዶና የክህሎት ሳምንት ሰልጣኞቻችንና የዚህ ውድድር ተሳታፊዎች ከሙያዊ የክህሎት ውድድሩ ጠቃሚ እውቀትና ልምድ በመቅሰም ሙያው የሚጠይቀውን የስነ-ልቦና ዝግጅትና ሥነ-ምግባር አሟልተው የሥራ ክቡርነት በመገንዘብ ሥራ ሳይመርጡ የሚሰማሩበትና ቀጣይ ህይወታቸውን በብቃት ለመምራት ብሎም የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል በዚህ አጋጣሚ ሰፊ ዕድል የሚያገኙበት ይሆናል ብለዋል፡፡
የክህሎት ውድድሩ በውጪ ቋንቋዎች (በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በጀርመንኛ) በምግብ ዝግጅት፣በመስተንገዶ፣ እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮች የተሳተፉበት ኤግዚብሽንና ሥራና ሰራተኛን የሚያገናኘው Job Fair ዋናዋና ፕሮግራሞች ሲሆኑ የፓናል ውይይቱ በነገው ዕለት በገነት ሆቴል የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመጨረሻም በተቋሙ ሰልጣኞች የተሰራውን ባህላችንን፣ አብሮነታችንን እንግዳ የምናስተናግድበትን ቡና በረከቦት፣ ስኒና ጀበና ከነቄጤማው የሚያሳየውን ኬክ ክብርት ሚኒስትርና የተቋማችን ዋናዳይሬክተር ከእንግዶች ጋር ሆነው ቆርሰዋል፡፡