በዘጠኝ ወራት ውስጥ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል፡፡የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የዳመጠ ሲሆን፤ የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች አቅርበው ሚኒስትሯ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት፤ በግብርናው፣ በአገልግሎት እና በኢንዱስትሪው ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡በሀገር ውስጥና ውጭ ሀገራት ዜጎችን በማሰልጠን እና በማብቃት በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተሰራው ስራ ውጤት ማምጣት መቻሉን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ ተቋሙ የመንግስትን የአገልግሎት ማሻሻያ የሪፎርም ትግበራ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጣራ እንዲሁም ተቋሙ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሰራው ስራ በጥንካሬ አንስተዋል፡፡
ለውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ በይበልጥ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ ተኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡የሥራና አሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር በተያያዘ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በበይነ መረብ እየሰጠ ያለው አገልግሎት እና የሪፎርም ስራዎች የሚበረታቱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ሁሉንም አካባቢዎች ታሳቢ ያደረገ ለዜጎች ፍታሃዊ የሆነ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ፤ ወደ ውጭ ሀገራት የሚሰመሩ ዜጎች ሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡ህግ እና ስርዓትን ተከትለው በማይሰሩ ኤጀንሲዎች ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መውስድ እንዳለበትም መግለፃቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
ምንጭ Ethiopian Broadcasting Corporation


Recent Comments