(ሆሳዕና :-የካቲት 05/2017)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት በክልሉ የሚገኙ መስህብ ስፍራዎች ላይ የተካሄደ የቱሪስት ጋይድ ማፕ እና ቱሪዝም ፓኬጅ ጥናት ሰነድ ላይ በሃላባ ቁሊቶ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።
የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ካርታ፣ አማራጭ የጉዞ ጥቅሎች እና የክልሉ ባህላዊ ምግቦች ላይ ጥናት መደረጉ ተገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር ባደረጉት ንግግር በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት እና በማስተዋወቅ ረገድ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ አበርክቶ ከፍ እንዲል እየተሰራ ነው ብለዋል።ጥናቱ በቀጣይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ካሉበት ስፍራ ሆነው የክልሉን መስህብ ስፍራና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቀላሉ የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።የቱሪዝም ዘርፉን በማዘመን ክልሉን የውስጥና የውጭ ቱሪስት ስበት ማዕከል የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሀላፊው ተናግረዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማማከር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም ተቋሙ የምርምር ፣ የማሰልጠንና የማማከር ስራ በመስራት የቱሪዝም ዘርፉን ተወዳዳሪ በማድረግ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ የበርካታ ታሪካዊ ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ቅርስ ባለቤት መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ እነዚህን አልምቶ የመጠቀም ውስንነት መኖሩን አንስተዋል።
ጥናቱ ቱሪስቶችንና የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ወጪ ቆጣቢ የሆነ ምቹ አገልግሎት ማግኘትና መስጠት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል ።
በመድረኩ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለን ጨምሮ ፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ሀላፊዎች እንዲሁም የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ባለሞያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በክልሉ ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚረዱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።
በኤልያስ ቲርካሶ