ስለ ሆ.ቴ.ሥ.ማ.ኢ. /Historical Background

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አመሠራረት
እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓ.ም. ከቅኝ ግዛት ነጻ የሚወጡ አገራት ያላቸውን ያልተበከለ የተፈጥሮ አካባቢና ባህል ተጠቅመው ቱሪዝምን በማልማት ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሳድጉ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ዕቅድ መሠረት የ1960ዎቹ አሥር ዓመት ለቱሪዝም ልማት እንዲሆን ተወስኖ እንቅስቃሴ ተደረገ፡፡
በመሆኑም በቱሪስት ድርጅት የቱሪዝም አማካሪ የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ሚስተር ዴቪድ ኤፍራት በቱሪዝምና ሆቴል ስልጠና እስራኤል እንድትረዳ ስምምነት እንዲዳረስ አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት፤ በራስሆቴልውስጥየመማሪያ ክፍሎችን በመከራየት በ1961 ዓ.ም. /1969 እ.ኤ.አ/ መጨረሻ የሆቴልናቱሪዝምሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሚል ስያሜ ስልጠናው ተጀመረ፡፡
በጊዜው በቱሪስት ድርጅት ውስጥ በነበሩት የሥራ ኃላፊዎችና በእሥራኤሎቹ ግፊት መንግስት ትኩረት ሰጥቶበት እስከ አሁን ማሰልጠኛው የሚጠቀምበት የሜክሲኮው ሕንጻ ተገነባ፡፡ሥራ ማስኬጃ በጀትም ተመድቦ በኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅት ሥር ሆኖ የቱሪዝም አማካሪ የነበሩት ሚስተር ዲቪድ ኤፍራት የትምህርትቤቱ ዳይሬክተር እንዲሆኑና ሌሎች እስራኤላውያን ኤክስፐርቶች በእንግዳ አቀባበል፣ በቤት አያያዝና በምግብና መጠጥ መስተንግዶ መሠረታዊ የአንዳንድ ዓመት ሥልጠና መስጠት ጀመሩ፡፡

በየሆቴሎቹ ያሉትን ሠራተኞች የአጫጭር ጊዜ የሙያ ሥልጠና መስጠት፣ ታክሲ ነጂዎች እንግዶቹን ሲያስተናግዱ የቋንቋ ችሎታቸውን በማሻሻል ተገቢውን የእንግዳ እንክብካቤ እንዲያውቁ ሥልጠናዎችን ይሰጥ ነበር፡፡
እንዲሁም ወጣት ተማሪዎችን በመደበኛ ፕሮግራም በማሰልጠን የቱሪስት አገልግሎቱን ለማሟላት ጥረት ተደርጓል፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዙሪያ የማያቋርጥ ጥናት ማካሄድም አንዱ የዓላማው ክፍል ነበር፡፡
በደርግ ዘመነ መንግስት
በ1967ዓ.ም. በሕብረተሰብ ትምህርት መምህርነት በተቀጠሩ ሰው አማካኝነት የመጀመሪያው የቱሪስት አስጐብኚነት የአንድ ዓመት ሥልጠና እንዲሰጥ ተደረገ፡፡
የ1967 ዓ.ም. በነበረው የመንግስት ለውጥ ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ በጥቂቱም ቢሆን የአወቃቀር ለውጥ እንዲኖረው አስገድዶታል፡፡
ትኩረቱ በየክፍለ ሀገሩ በሚገኙ የግልና የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሠራተኞችና አሠሪዎች /ከ5-15 ቀናት የቆዩ/ የሙያ መተዋወቂያ ሴሚናሮች ይሰጥ ነበር፡፡
ከዚያም ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው እቅድና የሰው ሀይል ፍላጐት መሠረት ለሆቴል ኮርፖሬሽንና ለብሔራዊ አስጐብኚና የጉዞ ወኪል ድርጅት የሚሆኑ ባለሙያዎችን ማሰልጠኑን በመደበኛና በሙያ ማሻሻያ አጠናክሮ ቀጠለ::
በዚህም አራት የአንድ ዓመት ሥልጠናዎች / ቱሪስት አስጐብኚነት በአንድ ዓመት ሥልጠና ዲፕሎማ እንዲሰጣቸው የሚገቡትም የኮሌጅ ዲፕሎማ እንዲኖራቸው የተወሰነ ነበር አንድ የሁለት ዓመት ስልጠና ማለትም በምግብ ዝግጅት እንዲሁም በሶሳቱም ሙያዎች የ3 ወራት የአጭር ጊዜ ስልጠና ሲለበስ ተዘጋጅቷል፡፡
ይህም አዲስ ሲለበስ የማስተማሪያ መርጃ መሣሪያዎችና እንደ ተማሪ መማሪያ የሚያገለግሉ መጽሐፍት መገኘት የሥልጠናውን ጥራት ለመጠበቅ በእጅጉ ረድቷል።
በኮሚሽኑና በስዊስ መንግስት መካከል በተደረገ የስልጠና ስምምነት 12 በልዩ ልዩ የሆቴል ሙያ አሰልጣኞችን ወደ ስዊዘርላንድ ተልከው በሚያስተምሩት ሙያ ለ16 ወራት የተጠናከረ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
በኢንዱስትሪው በተለይ በሆቴል ሥራአስኪያጅነት የሰው ኃይል እጥረትን ለመቀነስና የነባር ሠራተኞችን ሞራል ለመጠበቅ በተነደፈ እቅድ መሠረት ከአሥራ ሁለተኛ ክፍል በላይ ትምህርት ኖራቸው በሆቴል ሥራ ረጅም ጊዜ ያገለገሉትንና ከዩኒቨርስቲ በዲግሪ ተመርቀው የተቀጠሩትን ሠራተኞች በልዩ ጥናት በተዘጋጀ ሲለበስ የተጠናከረ የ6 ወራት የሆቴል ሱፐርቫይዘር ሥልጠና አሰጣጥሥራ በ1979 ዓ.ም. ተጀምሮ በርካታ የኢንደስትሪው ሰዎች በጊዜው ከነበሩት የመንግስት ሆቴሎች መጥተው ሠልጥነዋል፡፡
በዘመነ ኢህአዲግ
የኢፌዲሪ መንግስት ደርግ ከስልጣን ከወረደበት ጊዜ አንስቶ የኢንቨስትመንትና የነጻ ኢኮኖሚ ሥርዓት በአገራችን በማስፈኑ ብዙ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት (ሆቴሎችሬስቶራንቶች፣ ሎጆች፣ ሞቴሎች፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ ቡና ቤቶች የቱሪስት አስጐብኚ ድርጅቶች፣ የጉዞ ወኪሎችና
ወዘተ…) በየጊዜው እያደጉ መምጣት በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጐቱን እየጨመረው በመምጣቱ ይህ ማሰልጠኛም በተገኘው እድል በመጠቀም በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ኢንደስትሪውን ሲያግዝ ቆይቷል፡፡
በዚህም መሠረት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስም ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንደኛው ሆኖ አገልግሎቱን ለመስጠት የማያቋርጥ ጥረት እያደረገ፤መንግስትለቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት ምክንያት ማሰልጠኛው ተስፋፍቶ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት እንዲችል ለማድረግ የገነት ሆቴልንና ግቢውን በ1989 ዓ.ም በወቅቱ የማሰልጠኛው የበላይ አካል ለነበረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን አስረክቧል፡፡
የሆቴሉን የመኝታ ክፍሎች ወደ ማሰልጠኛ ክፍሎች ለመቀየር የሚያስችል የእድሳት ሥራ ተከናውኖ የመማር ማስተማሩ ሥራ እንደቀጠለ ነው ቢሆንም በቅርብ ጊዜም የመለማመጃ ሞዴል ሆቴል ግንባታ ይጀመራል እየተባለ ጥናቱ ተጠናቆ ባለአምስት ኮከብ ሞዴል ሆቴል ለመገንባት የተያዘው እቅድ ተግባራዊ ሳይደረግ እስካሁን ቆይቷል፡፡
የማታ ትምህርትን በተመለከተ 1981 ዓ.ም.
በአራት የትምህርት ዘርፎች ተጀምሮ የነበረውን የማታ ትምህርት ይበልጥ በማጠናከር የረጅም ጊዜ /የ1፣2 እና 3 ዓመት/ እና የአጫጭር ጊዜ /ከአንድ ወርእስከ ሶስት ወራት/ ስልጠናዎችን በመስጠት በስራ ላይ የሚገኙ የኢንደስትሪው አባላትም ሆኑ አዳዲስ ሙያውን ለማወቅ ጉጉት ያላቸውን ዜጐች በመርዳት ላይ ይገኛል፡፡
የሆቴልና የቱሪዝም አገልግሎትን አሁን ከደረስንበት የተገልጋይ ፍላጐት ጋር ለማስኬድ የሚያስችል ስልጠናዎች ካሪኩለም በማሰልጠኛው ባለሙያዎች ተቀርጾ እና በባለድርሻ አካላት ዳብረው በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ማሰልጠኛዎች ሁሉ እንዲጠቀሙባቸው እየተደረገ ነው፡፡
የመማር ማስተማሩን ሂደት የበለጠ እንዲያተጋውና ተማሪዎችም ትምህርቱን በተረጋጋ ሁኔታ የመቀበል አቅማቸው በገንዘብ ድጋፍ እንዲጠናከር እንዲዳብር ለማድረግ ቀድሞ ለተማሪዎች ይሰጥ የነበረውን አነስተኛ የኪስ ገንዘብ ምንም እንኳ አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ በቂነው ባይባልም በወቅቱ ከሌሎች የመንግስት ኮሌጆች ጋር አንድዓይነት እንዲሆን በእዚህም ብዙ ወጣቶች ወደ ሙያው ለመምጣት ያላቸውን ፍላጐት እንዲያነሳሳ ረድቷል፡፡
ማሰልጠኛው በሕግ ተቋቁሞ ተገቢውን ተግባር እንዲፈጽም በአዋጅ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቷል፡፡ የቴክኒክና ሙያ የኮሌጅ ደረጃ ያለው ማሰልጠኛ ሆኗል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ወደ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ስያሜውን ቀይሯል ተጠሪነቱ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሆኗል፡፡
ጥራት ያለው _ ስልጠና ስለመስጠት
የተቋሙ አቅሙን በማሳደግ በሙያው መምህራን እንዲገነባ ከመደረጉም በላይ ቀጣይነት ባለው የከፍተኛት ምህርት ስልጠና መምህራን እውቀታቸውን እንዲያሳድጉም እየተደረገ ይገኛል፡፡ ተቋማችን በአሁኑ ጊዜ በስምንት የሙያ መስኮች ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የስልጠና መስኮች በአዲስ መልክ ተዘጋጅቷል፡፡
በሆቴል አስተዳደር
በቱሪዝም አስተዳደር
በደረጃ አራት
1. በእንግዳ አቀባበል
2. በቤት አያያዝ
3. በምግብና መጠጥ ቁጥጥር
4. በምግብና መጠጥ መስተንግዶ
5. በኬክ ዝግጅት
6. በቱሪስት አስጎብኝ
በደረጃ አምስት
7. በክሉናሪ አርት(በምግብ ዝግጅት )
8. በቱርኦፕሬሽን

በተቋማችን በሁለቱም የሙያ ዘርፎች እስካሁን 20ሺ የመደበኛና ተከታታይ የተምህርት ክፍል የተመረቁ ሲሆን ሆኖም በየዓመቱ ከሚሰለጥኑ የሥራ ላይ ስልጠና የሚያገኙትን አያካትትም፡፡
የተግባር ትምህርትን በተመለከተ የሆቴል ሰልጣኞች በተግባር በተቋሙ ከሚያገኙት ሥልጠና ባሻገር በከተማው የሚገኙ ባለኮከብ ሆቴሎች የትብብር ስልጠና ያገኛሉ፡፡ የቱሪዝም ሰልጣኞች በቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎቻችን በሶስት አቅጣጫ ሙሉ መዳረሻዎቻችን ከመምህራን ጋር በመጎብኘት የተግባር ሥልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም በአስጎብኝ ድርጅቶች አማካኝነት የትብብር ስልጠና ያገኛሉ፡፡
ተቋሙ በአሁኑ ጊዜ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት መሰረት ያደረገ ስልጠና የሚሰጥባቸውን የሙያ መስኮች ደረጃ በማሳደግና በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ አካል የሆነ የተቋሙን ስልጠና ደረጃ ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል ISO 21001/2018 አንዱ ነው፡፡
ሌላው በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንደስትሪውን በጥናትና ምርምር መደገፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን ዘንድሮ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያላቸውን አስተዋጽኦ የዳሰሰ ጥናት መሰራቱ ነው፡፡
በዘርፉ ስልጠና የሚሰጡ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎቻችን በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
መንግስትም ተቋሙን በበጀት በመደገፍና ተጠሪነቱን ለሥራና ህህሎት ሚኒስቴር አድርጎ በአዲስ መልክ ሲያደራጀው ቱሪዝም ዘርፉን የሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ላይ በሰፊው እንዲሰራ ከማቀድ አንጻር መሆኑ ዕሙን ነው፡፡
ቱሪዝም ዘርፉ አገራችን ካላት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህብ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ አንጻር ምንም ያልተሰራበት በመሆኑ ዘርፉን መደገፍና በዘርፉ የሰለጠነና የበቃ የሰው ወጣት ኃይል ማፍራት ልንመልሰው የሚገባን የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡
ስለሆነም ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ጊዜ የከፍተኛ ትምህርት ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶ የመማር ማስተማሩ ሥራ ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም እስካሁን የማቋቋሚያ ደንቡ አልጸደቀም በዚያ ምክንያት የተቋሙን መዋቅር መስራት አልተቻለም፡፡
በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎችን ያፈራ ለአገራችን ብሎም ከምስራቅ አፍሪካ ጭምር ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችል ተቋም በማሳደግ መንግስትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱ መልካም ነው፡፡