ኢንስቲትዩቱ ከዌልነስ ሜዲካል ኮሌጅ ጋር አብሮ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከዌልነስ ሜዲካል ኮሌጅ ጋር አብሮ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ በመገኘት የፈረሙት የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደገለፁት የኢንስቲትዩቱ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠና ከመላው ሀገሪቱ መጥተው የሚሰለጥኑበት መሆኑን በመጥቀስ ይህ ስምምነት ወቅቱ የሚፈልገውን የስፓና የማሳጅ አገልግሎት የሚሰጡ ስልጡን ባለሙያዎችን ለማፍራት ዓላማ እንዳለው ገልፀዋል።
የዌልነስ ሜዲካል ኮሌጅ ባለቤት ዶ/ር ሰላም አክሊሉ በበኩላቸው ስልጠናው በሀገር ደረጃ በቱሪዝም ዘርፍ እንዲሰጥና በየሆቴሎቹም የሚገኙ ባለሙያዎች ይህን ስልጠና ሳይወስዱ እንዳይሰሩ መደረግ እንዳለበት፣ ለዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን አንስተዋል። በሆቴልችና በአንዳንድ ቦታዎች እየተሰጡ ያሉ የማሳጅ አገልግሎቶች የሀገርን ስም ከማጉደፋቸው ባሻገር የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያለው ተፅእኖ ቀላል አይደለም ብለዋል።
ከዌልነስ ሜዲካል ኮሌጅ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በስልጠና ዘርፍ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜም በአጫጭር ስልጠና ዘርፍ የስድስት ወር ስልጠና የሚጀምሩ ይሆናል።
በቀጣይ የሰልጣኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ወደ ደረጃ የማሳደግ ፍላጎት መኖሩን የስልጠናና አቅም ግንባታ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት ተናግረዋል።
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/