የሰልጣኞቻችን ምረቃ
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የ58ኛ ዙር ሰልጣኞችን አስመረቀ
የኢፌዲሪ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት በዲግሪ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በደረጃ (ሌቭል) ያሰለጠናቸውን የ58ኛ ዙር 350 ባለሙያዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል።
የኢንስቲትዩቱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው፤ ምርቃቱ የላቀ የኃላፊነት ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ያለው ዓለም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ በቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተቀየረ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፣ ተመራቂዎች ከተቋሙ ከወጡ በኋላም መማርን ሳያቆሙ እውቀታቸውንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በቀጣይነት በማሳደግ በገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
አያይዘውም ወጣቶች የሀገሪቱን ሰላም፣ መቻቻልና ብሔራዊ አንድነት የማጠናከር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፣ የሆስፒታሊቲ ዘርፍ ስኬት መሠረቱ የሰዎች ቀና መስተንግዶ፣ ፈገግታና የላቀ አገልግሎት መሆኑን አብራርተዋል።
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትና ባሻሻላቸው አዳዲስ መዳረሻዎች ምክንያት በበጀት ዓመቱ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውንና ይህም ካለፉት ዓመታት የላቀ ጭማሪ ማሳየቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ተመራቂዎችም የሀገሪቱን መልካም ታሪክና እሴት ለዓለም የሚያስተዋውቁ እውነተኛ የባህል አምባሳደሮች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።
ይህ የ58ኛ ዙር 350 ባለሙያዎች ምርቃት ሀገሪቱ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላትና የአገልግሎት ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።
ሰኔ 11/2018 ዓ.ም፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ለወቅታዊ ትኩስ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
Official Website: mols.gov.et
Facebook: https://web.facebook.com/MolsFDRE
Telegram: https://t.me/FDRE_MoLSofficial
TikTok: tiktok.com/@mols_official
Twitter / X: twitter.com/Jobs_ሚኒስቴር
WhatsApp: whatsapp.com/channel/0029VakCgcYI See less