ኢንስቲትዩቱ በደሴ ከተማ 500 የሆቴል ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀመረ፤
ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም
ቱ.ማ.ኢ
የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራትና የኢንዱስትሪውን የአገልግሎት ጥራት በማሳደግ ረገድ የተሰጠውን ተልዕኮ መሠረት በማድረግ በደሴ ከተማ ለሚገኙ 500 ያህል የተለያዩ የሆቴል ባለሙያዎች የሥራ ላይ ስልጠና መስጠት ጀመረ።
በደሴ ከተማ መስጠት የተጀመረው ስልጠና፣ ኢንስቲትዩቱ የሀገራችንን የቱሪዝም ዘርፍ በሰለጠነ የሰው ኃይል በመደገፍ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ደረጃ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ራዕዩ አካል እንደሆነ ተገልጿል።
የስልጠናውን መጀመር አስመልክተው የደሴ ከተማ ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መመሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው እንደገለጹት በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የቱሪስት ፍሰት በላቀ ደረጃ ለማስተናገድና የደንበኞች አያያዝን ለማሻሻል ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር ይህ ዕድል መመቻቸቱን ተናግረዋል።
አክለውም ሆቴሎቻችን የበለጠ እንግዳ ተቀባይና የላቀ አገልግሎት ሰጪ ከሆኑ ለከተማችን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
የስልጠናው አስተባባሪዎች አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ተመስገን በቀለ በመስተንግዶው ዘርፍ የሚታየውን የእውቀትና ክህሎት ክፍተት በመሙላት ረገድ በሥራ ላይ የሚሰጡ ተከታታይ ስልጠናዎች የቱሪስቶችን ፍሰት ዘላቂ በሆነ መንገድ እንዲጨምር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ሀገራችን ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት ውጤታማ ለማድረግ በክህሎት የበለፀገ የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ በመሆኑ ኢንስቲትዩቱ ይህንን ዓላማ ለማሳካት በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ስልጠናው በሁለት ፈረቃና በሰባት ቡድኖች ተከፍሎ ለሦስት ቀናት በኢንስቲትዩቱ አሰልጣኞች ይሰጣል።
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም፡https://t.me/tticommunication
http://tiktok.com/@ftti_official See less